የሐሙስ መረጃዎች: የሳምንቱ አጫጭር ኪናዊ መረጃዎች
☑️መጽሐፍ
-የአንጋፋው ደራሲ ፍቅር ማርቆስ ደስታ”የሚሳም ተራራ” የተሰኘ የግለ ታሪክ መጽሐፍ ከመጋቢት 16 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሀገር ውስጥ አንባቢያን አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት በኩል ይደርሳል ተብሏል።በዚህ ሳምንት ደራሲ ፍቅር ማርቆስ ደስታ”የሚሳም ተራራ” የተሰኘ የግለ ታሪክ አዲስ መጽሐፍ በአማዞን የሽያጭ ሰንጠረዥ በአፍሪካ ሥነጽሑፍ ከወጡት አዳዲስ መጻሕፍት ቀዳሚውን ቦታ በመያዝ እየመራ እንደነበር ይታወሳል።
-የደራሲ ማስረሻ ማሞ “አባት አልባ ህልሞች” መጽሐፍ በቀጣይ ወር ሚያዝያ 13 2016 ዓ.ም( April 21)በኔዘርላንድ ሀገር ኡትረክት ከተማ ውስጥ ይመረቃል። በዚህ የመጽሐፍ ምርቃት ዝግጅት ላይ ዶ/ር አዜብ አመኅ እና አቶ መስፍን አማን የመጽሐፍ ዳሰሳ ያቀርባሉ ተብሏል።
☑️ሙዚቃ
-ድምጻዊ ባልከው አለሙ እና ድምጻዊት ስንታየሁ በላይ “ከሀሳቤ” በሚል ርዕስ በቅብብሎሽ የሰሩትን ሙዚቃ ነገ አርብ በሙዚቃዊ ሪከርዲንግ በኩል ለአድማጮች ያደርሳሉ። ባልከው እና ስንታየሁ በቅርቡ”የኔ ዓለም” እንዲሁም “ፀደይ” የተሰኙ ገሚስ አልበሞችን ለአድማጮች አድርሰዋል።
-አድናቂዎች “የኢትዮ ጃዝ አባት”ሙላቱ አስታጥቄን በአካል አግኝተው ፍቅራቸውንና አድናቆታቸውን የሚገልፁበት ፕሮግራም የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 14 2016 ዓ.ም በአፍሪካ ጃዝ ቬሌጅ ተዘጋጅቷል።በዕለቱም ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ የህይወት ልምዳቸውን ያጋራሉ፣ ከአድናቂዎቻቸው ጋር የፎቶ ሥነሥርዓት ፣ ፊርማ ፣ የሙዚቃና የእራት ግብዣ ዝግጅቶች ይኖራሉ ተብሏል።
☑️ቴአትር
-አርቲስት ድርብወርቅ ሰይፉ እና አለልኝ መኳንንት ፅጌ”የፍቅር ካቴና” በተሰኘ ተውኔት ከበርካታ ዓመታት በኃላ በድጋሚ ወደ ቴአትር ሊመለሱ እንደሆነ ተሰምቷል። በአርቲስት ወይንሸት አበጀ ፕሮዲዩስ የተደረገው ይህ “የፍቅር ካቴና” ተውኔት ድርሰትና ዝግጅቱ የአለልኝ መኳንንት ፅጌ ነው።በተውኔቱ ላይ ከአርቲስት ድርብወርቅ ሰይፉ በተጨማሪም ሚኪ ተስፋዬ ፣ ወይንሸት አበጀ ፣አሸናፊ ማህሌት በተዋናይነት ይሳተፉበታል።በቅርቡም ተውኔቱ ለመድረክ ይበቃል።
-“እብደት በህብረት” የተሰኘው የአንድ ተውኔት በቋሚነት ዘወትር ሀሙስ በ12:00 እና እሁድ በ8:00 በዓለም ሲኒማ መታየት ጀምሯል።”ዕብደት በሕብረት” የአንድ ሰው ተውኔት በቶፊቅ ኑሪ ተደርሶ በዳግማዊ አመለወርቅ ፊይሳ የተዘጋጀ ተውኔት ነው።ተዋናይ አማኑኤል ሀብታሙ የሚተውንበት”እብደት በህብረት” ተውኔት መቼቱን በሶስት መንግስታት ሥርዓት ላይ አድርጎ ከገፀ-ባህሪው ማንነትና ትዝታ ጋር ተመልካችን በማቆራኘት ይጠይቃል ይጎሽማል ያስቃል ያዝናናል ተብሏል።”እብደት በህብረት” የአንድ ሰዉ ተውኔት ሲሆን ባልተለመደ መልኩ “ተረፈ”የተሰኘ ድመት አብሮ ተውኖበታል።
-“የአባወራ ጉዞ”ተውኔት የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 14 2016 ዓ.ም ከቀኑ በ8:00 በሐዋሳ ሲዳማ ባህል አዳራሽ ይመደረካል። የተውኔቱ ደራሲ አርተር ሚለር ፣ ትርጉም ዓለማየሁ ገ/ህይወት አዘጋጅ ተክሌ ደስታ ፣ ረ/አዘጋጅ ተስፋዬ ገ/ሐና ናቸው።በተውኔቱ ላይ ተስፋዬ ገ/ሐና ፣ ሐኖክ በሪሁን፣ ሚካኤል ታምሬ ፣ሱራፌል ተካ ፣ትዕግሥት ባዩ፣ ገነት አሰፍ ፣አሳዬ ገነነና አለማየሁ ገ/ህይወት ይሳተፉበታል። ይህ ተውኔት በአሜሪካ ኤምባሲ ስፖንሰር ተደርጎ ከዚህ ቀደም በጅማ በባህርዳር በጎንደር እና ብሔራዊ ቴአትር ታይቶ ነበር።ቅዳሜ በሀዋሳ ከተማ በ8:00 እና ሰኞ አመሻሽ ላይ ለሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በነፃ ይቀርባል።
☑️ሥነጥበብ (ሥዕልና ተያያዥ ጥበባት)
-የሠዓሊ መርዕድ ታፈሰ “ልዕልት” የሥዕል አውደርዕይ መጋቢት 6 2016 ዓ.ም ጎላ ፓርክ በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ በቅቷል።
በዚህ አውድርዕይ የሠዓሊ መርዕድ ታፈሰ የ25 ዓመታት የሥዕል ስብስቦችን ያካተቱ ከ150 በላይ የሥዕል ስራዎች ቀርበዋል። ይህ የሥዕል አውደርዕይ እስከ መጋቢት 27 2016 ዓ.ም ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል።
-የሠዓሊ አሸናፊ ወልደየስ “Voyage and migration of birds” የተሰኘ የሥነጥበብ አውደርዕይ ባሳለፍ ወር የካቲት 28 2016 ዓ.ም ስድስት ኪሎ በሚገኘው ገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ ለእይታ ይበቃል። ይህ የሥነጥበብ አውደርዕይ እስከ መጋቢት 29 2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል።
☑️በቅርቡ ለእይታ የሚበቁ የሥነጥበብ አውደርዕዮች
-ላፍቶ የሥዕል ማሳያ INSPIRED WOMEN በሚል ርዕስ የሚያዘጋጀውን የሥነጥበብ ዓውደርዕይ በዚህ ዓመትም ለ5ኛ ጊዜ “INSPIRED WOMEN 5 “በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ አንጋፋና ወጣት ሴት ሠዓሊያን የሚሳተፉበት የሥነጥበብ ዓውደርዕይ የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 14 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:30 ጀምሮ በላፍቶ አርት ጋለሪ በይፋ ይከፈታል::
-የሠዓሊ አልሪኬ አልጋይር “ቃል ድምጽና ምናብ” የተሰኘ የሥነጥበብ አውደርዕይ መጋቢት 16 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ በፈንድቃ ባህል ማዕከል ለእይታ ይበቃል። ይህ ሥነጥበብ አውደርዕይ እስከ መጋቢት 30 2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
አዘጋጅ: ናቲ ማናዬ
መጋቢት 12 2016 ዓ.ም