የሐሙስ መረጃዎች: የሳምንቱ ኪናዊ መረጃዎችን በአጫጭሩ
1.ከተለመዱት ዘውጎች ወጣ ያለ የፊልም ይዘት ይዞ የመጣው “6:00 ሰዓት ከሌሊቱ ” ፊልም ባሳለፍነው ሰኞ ተመርቋል።ይህ የትሪለር ዘውግ ያለው ፊልም ከሰባት በላይ ቦታዎችን መቼቱ አድርጓል። ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት ገደማ የፈጀ ሲሆን ፤ አርቲስት ሠላም ተስፋዬ ፣ አርቲስት ሚኪ ተስፋዬና ሌሎች የፊልም ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። በሀይሉ እንግዳ የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ሲሆን በሀይሉ እንግዳ እና በሸነና ቦሩ የፊልሙ ኤክኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች ናቸው። መጋቢት 6,7,8 እንዲሁም መጋቢት 13, 14 , 15 በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች መታየት ይጀምራል።
2.የኮሜዲያን እሸቱ መለሰ “ማን እንደ ሀገር ” የተሰኘ የኮሜዲ ዝግጅት የፊታችን ቅዳሜ መጋቢት 7 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ውስጥ ይካሄዳል።
3.”ዜሮ ዲግሪ” ፊልም በቅርቡ ለእይታ ይበቃል። በአልዓዛሬ ሣለልኝ ደራሲ እና ዳይሬክተርነት የተሰራው “ዜሮ ዲግሪ” ፊልም ከመጋቢት 20 ጀምሮ ለተመልካች ይቀርባል።በፊልሙ ላይ ሰለሞን ሙሄ ፣ ቸርነት ፍቃዱ ፣ ቃልኪዳን ጥበቡ ሌሎችም በተዋናይነት ተሳትፈዋል።
4.”ጦቢያ” በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ሊደገም ነው። የአድዋ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝግጅቱን ለማቅረብ ወደ እንግሊዝ ለንደን የተጓዘው “የጦቢያ ግጥምን በጃዝ” ቡድን የአድዋ ቀን ዝግጅቱን ማቅረቡ ይታወሳል።በታዳሚው ጥያቄ መሰረት የፊታችን መጋቢት 14 2016 ዓ.ም (ማርች 23 6:00 PM ) ድጋሚ እንደሚያቀርብ ከዝግጅት ክፍሉ ኤቨንት አዲስ ድረገጽ ሰምቷል።
5.በዘጠናዎቹ “አትፍራኝ አትሽሽኝ” በተሰኘው ሙዚቃዋ ተወዳጅ የነበረችው ድምጻዊት ቤተልሔም መኮንን በአዲስ የሙዚቃ ስራ ወደ ሙዚቃ ልትመለስ እንደሆነ ኤቨንት አዲስ ድረገፅ ሰምቷል።የዚህ ሙዚቃ ተንቀሳቃሽ ቪዲዮ በአንዱፖ ፊልም ፕሮዳክሽን በኩል ይሰራል ተብሏል።ድምጻዊት ቤተልሔም መኮንን በገጠማት የጤና እክል ምክንያት በቅርቡ በብዙሃኑ ዘንድ መነጋገሪያ እንደነበረች ይታወሳል።
6.መቅረዝ ሥነኪን የኪነጥበብ ፕሮግራም ዛሬ ይካሄዳል። ወር በገባ የመጀመሪያው ሀሙስ የሚዘጋጀው “መቅረዝ ሥነኪን” የኪነጥበብ ፕሮግራም ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 5 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል። አንጋፋው የተወኔት ሰው ተስፋዬ ሲማ በክብር እንግድነት በሚገኘበት ፕሮግራም ላይ ልዩ ልዩ ኪናዊ መሰናዶዎች በባለሞያዎች ይቀርባል ተብሏል።
7.በዛጎል መጻሕፍት ባንክ የሚዘጋጀው “ነገረ መጻሕፍት” የመጽሐፍ ውይይት የፊታችን ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ይካሄዳል። በዚህ ሳምንት ዝግጅት ከዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ ጋር “የመኢሶን ሰማዕታት ” መጽሐፋቸው ላይ ውይይት ይካሄዳል።የዕለቱ አወያይ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው። ይህ መርሐግብር ቅዳሜ መጋቢት 7 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 እስከ 10:30 ይካሄዳል።
8.የገጣሚ በረከት ተስፋዬ “የሰው መልክ” መጽሐፍ የፊታችን ሰኞ መጋቢት 9 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:30 ጀምሮ በሀገርፍቅር ቴአትር ቤት ይመረቃል።በዕለቱም አንጋፋና ወጣት የሥነጽሑፍ ባለሞያዎች ሀሳቦቻቸውን በመድረኩ ያቀርባሉ።ይህ መጽሐፍ የገጣሚው የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው።
9.የደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ “በዓለቱ ላይ ” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን መጋቢት 14 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 እስከ 12:00 ሰዓት በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል። በዕለቱም የተለያዩ የክብር እንግዶች ይገኛሉ ተብሏል።ደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም “የምወድህ”፣ “የእግዜር ዕዳ”ን ጨምሮ የተለያዩ መጻሕፍትን ለአንባቢያን አድርሳለች።
10.ከደራስያን ጋር የመጨዋወት እና መጽሐፍ የማስፈረም ልዩ ሥነ-ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ በዋልያ መጻሕፍት ይካሄዳል። የዚህ ሳምንት የክብር እንግዳ “ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች አስተዳደር” በተሰኘው መጽሐፍ ዶ/ር ዓይናዓለም አባይነህ እንግዳ ናቸው። ቅዳሜ መጋቢት 7 2016 ዓ. ም ከጠዋቱ 4:00 እስከ 6:30 ድረስ አራት ኪሎ በሚገኘው ዋልያ መጻሕፍት ውይይቱ ይካሄዳል።
11.የወመዘክር አውደርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያን ታሪክ በፎቶ የሚተርከው “በፎቶግራፎች ታሪክ ሲነበብ” በሚል ርዕስ ወመዘክርና Gerar-The Creative Hub በጋራ በመሆን የተዘጋጀው የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ የካቲት 16 2016 ዓ.ም ለእይታ ክፍት ሆኗል እስከ መጋቢት 15 2016 ዓ.ም ይቆያል።በሌላ በኩል “የዘመን ማሚቶ” የድምፅ ቅንብር አውደርዕይ እየተካሄደ ይገኛል።ይህም አውደርዕር እስከ መጋቢት 15 2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል።
12.”ማንነት” የተሰኘ የካሊግራፊ አርት አውደርዕይ ከፊታችን መጋቢት 14 እስከ 23 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሙዚየም የሥዕል ማሳያ ውስጥ ይካሄዳል።
አዘጋጅ: ናቲ ማናዬ
ቀን: መጋቢት 7 2016 ዓ.ም
Website: https://eventaddis.com/
Telegram: https://t.me/EventAddis1