የሳምንቱ ኪናዊ መረጃዎች (ሚያዝያ 17 2016 ዓ.ም )
የሙዚቀኛ ጆርጋ መስፍን አዲስ አልበም በግንቦት ወር ለአድማጮች ይደርሳል። የታዋቂው ሙዚቀኛ ፣ አሬንጀርና ፕሮዲውሰር ጆርጋ መስፍን ‘ከሁሉ የላቀው ደግ’ የተሰኘ አዲስ አልበም ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በዲጂታል መተግበሪያዎች ይለቀቃል ተብሏል።‘ ከሁሉ የላቀው ደግ’ በተለይም የኢትዮጵያ ጃዝ ሙዚቃ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ይዘቶች ጋር መንፈሳዊነትን በማዋሃድ ኢትዮ ጃዝን የሚያስቃኝ አልበም ነው ተብሏል።
“የነጋሪት ባንድ” ባንድ አልበም የፊታችን እሁድ ይመረቃል።የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሙዚቃን በአንድ የያዘው “ነጋሪት ባንድ” የሀገርበቀል የጃዝ የሙዚቃ አልበም የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 19 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ውስጥ ይመረቃል።በዕለቱም ተፈሪ አሰፋ ፣ ጆርጋ መስፍን ፣ አብይ ተክለማርያምን ጨምሮ የነጋሪት ባንድ ባልደረቦች የሙዚቃ ዝግጅታቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን መራዋ ኳየር እና የተመስገን ልጆችም ዝግጅታቸውን ከሚያቀርቡት ውስጥ ናቸው። ይህ ዝግጅት የመግቢያ ክፍያ የለውም።
የሙዚቀኛ ጣሰው ወንድም “የትንፋሽ ውበት” የተሰኘና በይዘቱ ለየት ያለ አቀራረብ አለው የተባለ የዋሽንት ሙዚቃ አልበም ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 17 2016 ዓ.ም Tasew Wendim በተሰኘው የዩቲዩብ ቻናል እና በተለያዩ የሙዚቃ መተግበሪያዎች ይለቀቃል።በአልበሙ ላይ በፒያኖ ቀረጻ እና ሚክሲንግ አብይ ወ/ማርያም ፣ በፐርክሽን ተፈሪ አሰፋ ፣በክራራ ቢኒያም ዳኛቸው ፣በቤዝ ክራራ እዮሲያስ ታመነ ተሳትፈዋል።
የመምህርት ዘቢብ መልኬ “ኮላዥ” የተሰኘ መጽሐፍ ነገ ዓርብ ሚያዚያ 18 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በግሩቨ ጋርደን ይመረቃል።መጽሐፉ በ228 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን የአጭር ልብ ወለድ ትረካዎች ስብስብ ነው ተብሏል።ደራሲዋ ቀደም ሲል “ስብጥር” የተሰኘ የግጥሞችና አጭር ልብወለዶች መድበል ያሳተመች ሲሆን “የፅጌ አበባ እና ሌሎች ተረቶች ” የሚል የልጆች መፅሀፍም አበርክታለች ።
-የጋዜጠኛ ሞሊቶ ኤልያስ “ሉዱንዳ” የተሰኘ አዲስ የጠቅላላ እውቀት መጽሐፍ ነገ አርብ ሚያዚያ 18 2016 ዓ.ም ከቀኑ ጀምሮ 10:00 በወመዘክር አዳራሽ፣ አንጋፋና ወጣት ደራሲያን የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።መፅሀፉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በቅርቡ ሆሳዕና ከተማም ይመረቃል። “ሉዱንዳ” መጽሐፍ በ17 ምዕራፎች ከ190 በላይ አስገራሚ መረጃዎች፣ አስደማሚ ክስተቶችንና ጠቃሚ መረጃዎችን ይዞ በ159 ገፅ በ300 ብር የጀርባ ዋጋ ለገበያ ይቀርባል።
-በደራሲ ባየህ ንጉሴ የተዘጋጀው “ፋሽን” የተሰኘ በፋሽን እና ሞዴሊንግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሐፍ ቅዳሜ ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ወመዘክር አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው የጥበብ ቤተሰቦች እና እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል ይመረቃል።በስድስት ምዕራፍ የተከፈለውና በ161 ገፆች የተነበበው መጽሐፉ በ298 ብር የጀርባ ዋጋ ለአንባቢያን ደርሷል። በተለያዩ የመጻሕፍት መደብሮች እንደሚገኘ ተገልጿል።
-“ሥነ-ተረት እና ፍልስፍና” የተሰኘ የሀሳብ ውይይት የፊታችን ሚያዝያ 18 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ 5 ኪሎ በሚገኘው አፄ ናኦድ ት/ቤት ግቢ ውስጥ ይካሄዳል። “ሥነተረት እና እና ፍልስፍና” በሚል ርዕስ በፀጋው ማሞ መነሻ ሀሳብ ይቀርባል ተብሏል።
-ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም የክብር የእንግዳ የሆነበት አንጋፋው የኪነጥበብ ምሽት አርብ ይካሄዳል።በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል የሚዘጋጀው የኪነጥበብ መርሃግብር ነገ አርብ ሚያዝያ 18 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11:30 ጀምሮ ይካሄዳል። በዕለቱ ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም “የአንድ ግጥም፣ የአንድ ወግ” የክብር እንግዳ ሆኖ ይገኛል።
-የሠዓሊ መሐሪ ተሾመ ፣ የሠዓሊ ሙሉ ለገሰ፣ የሠዓሊ አሌክሳንደር ታደሰ የሥዕል ስራዎች የቀረበበት በጊዜ እይታ ወይም “Through the eyes of time” የተሰኘ የሥነጥበብ አውደርዕይ ከባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 12 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወሎ ሰፈር ዳኒ ፕላዛ በሚገኘው አውሮራ የሥዕል ማሳያ ውስጥ በእይታ ላይ ይገኛል።
-የአኑማ ሀይሉ “ታሪክ እና ከዋክብት ” የተሰኘው የሥነጥበብ አውደርዕይ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 17 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ ቦሌ ዓለም ሲኒማ ጀርባ በሚገኘው አትሞስፌር ውስጥ ይከፈታል።ይህ አውደርዕይ እስከ ግንቦት 2 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነው።
-የሠዓሊ ወርቅነህ ብዙ “ፅድቅና ኩነኔ” የተሰኘ የሥዕል አውደርዕይ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 17 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ አትላስ በሚገኘው ኢትዮ ሜትሮፖሊታን የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ ይቀርባል ተብሏል። በመክፈቻው ሥነሥርዓት የተለያዩ የሥነጥበብ አፍሪቃውያን እና የሥነጥበብ ባለሞያዎች ይገኙበታል ተብሏል። አውደርዕዩም ለሳምንታት በእይታ ላይ ይቆያል።
አዘጋጅ: ናቲ ማናዬ
ሚያዝያ 17 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ