ድምጻዊት መክሊት ሀደሮ “ኢትዮ ብሉ” የተሰኘ ግሚስ የሙዚቃ አልበም ከሰሞኑ ለአድማጮች አድርሳለች
መክሊት ሀደሮ እንግሊዘኛ ቀመስ በሆነ አማርኛ፣ አፍሮዋን አበጥራ፣ መድረክ ላይ በወንበር ቁጭ ብላ ዳንስና ወግ በቀላቀለ አኳኋን ‹‹ከመከም ጎፈሬ›› የሚለውን ሀገርኛ ዜማ ስትጫዎት በብዙኃኑ አእምሮ ውስጥ ሰርጻለች፡፡
ስድስት ዜማዎችን የያዘ በዘመኑ ‹‹ግማሽ አልበም›› ተብሎ የሚታወቀውን ዓይነት አልበም ሰሞኑን ለአድናቂዎቿ ማድረስ የቻለችው መክሊት ይሄንን ሥራ ጀምሮ ለመጨረስ አምስት ዓመታት እንዳስፈለጓት ለኤፍ ኤም አዲስ የመሰንበቻ ፕሮግራም ዝግጅት ገልጻለች፡፡
ሥራው አምስት ዓመታት ሊፈጅ የቻለው አንድም የመጀመሪያ ልጇን ያገኘችው ከአራት ዓመታት በፊት በመሆኑ አንድም የኮቪድ ወረርሽኝ ብዙ ሥራዎችን ስላስተጓጎለ መሆኑን ገልጻለች፡፡
‹‹ኢትዮ ብሉ›› በሚል ስያሜ ለአድማጭ የቀረበው አልበሙ የአሜሪካዎቹ ጃዝና ብሉዝ የሙዚቃ ስልቶች ከኢትዮጰያ ባህላዊ ዘፈኖች ጋር ተዋህደው የቀረቡበት ሥራ መሆኑን መክሊት ትናገራለች፡፡
አብዛኛዎቹ ዘፈኖች የእርሷ ድርሰቶች መሆቸውን የገለጸች ሲሆን ዝነኛዋ ገጣሚና የተውኔት ሰው ዓለም ጸሐይ ወዳጆ ‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ›› የተሰኘውን ዘፈን ግጥም እንደጻፈችላትም ተናግራለች፡፡
ከዚህ አልበም በተጨማሪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አድማጭ የሚደርስ ሌላ አልበም እየሠራች መሆኗን የገለጸችው መክሊት ይሄንን አልበም ለመሥራት ሲባል በቅርብ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እቅድ እንዳላት ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ለመሰንበቻ ፕሮግራም ይፋ አድርጋለች::
ዘገባው የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ነው
ለተጨማሪው:https://t.me/EventAddis1