የሐሙስ መረጃዎች: አጫጭር የሳምንቱ ኪናዊ መረጃዎች
በናቲ ማናዬ
☑️ድምጻዊት ዘቢባ ግርማ በቅርቡ አዲስ አልበም ለአድማጮች እንደምታደርስ አስታወቀች ።ለአልበሙ መዳረሽ እንዲሆንም “ስሜን በስሙ” የተሰኘ አዲስ ሙዚቃ ነገ ለአድማጮች ታደርሳለች። የሙዚቃው ግጥም የአብዲ ራህዋ ሲሆን ዜማውን አለማየሁ ደመቀ ሙዚቃ ቅንብሩን ፋኑ ጊዶቢ ሰርቶላታል።
☑️ድምጻዊት የማርያም ቸርነት (የማ) አስቀድማ በማርዮት ሆቴል ካቀረበችው የመድረክ ስራዎቿ መካከል አራት ሙዚቃዎችን ዛሬ ሐሙስ የካቲት 28 2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በ”የማ” የዩቲዩብ ቻናል ለአድማጮች ታደርሳለች። የሚለቀቁት “የደጋ ሰው” “ራያ” “ሾምቢቴ” “ጋሻዬ ክብሩ ” የተሰኙ ሙዚቃዎቿ ናቸው።
☑️የድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ (አርዲ ) በቅርቡ ከተለቀቀው “አስቻለ” የሙዚቃ አልበም ላይ የተወሰደ አዲስ የሙዚቃ ቪዲዮ ነገ አርብ ለሙዚቃ አድማጮች ይደርሳል።
☑️የሙዚቀኛ ካሥማሠ “ሰዋሰው” የሙዚቃ ኮንሰርት አርብ የካቲት 29 2016 ዓ.ም በዘ ቬንዩ ዌርሀዉስ ይካሄዳል። ከካሥማሠ ጋር በመሆን ኩል ሱሬ ፣ ማህሌት ነጋሽም ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።
☑️ ድምጻዊት ሲሳይ ጌታሁን ከዙምባራ ባንድ ጋር በመሆን የተጫወተችው ‘’አዲስ ቀን’’ የተሰኘ የሙዚቃ ቪዲዮ በነገው ዕለት በሙዚቃዊ ዩቲዩብ ቻናል እንዲሁም በሁሉም የዲጂታል የሙዚቃ መተግበሪያዎች ይለቀቃል፡፡
☑️የደራሲ አለማየሁ ደመቀ “ዮቶር ሁለት” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በቅርቡ ለአንባቢያን ይደርሳል። የመጀመሪያው “ዮቶር ኮብላይ ካህን” የተሰኘው መጸሐፍ ከሰሞኑ 14ኛው ዕትም ለአንባቢያን ቀርቧል።
☑️የደራሲ ፍቃዱ አየልኝ “ግርባብ ያ ደግ ሰው” የተሰኘ መጽሐፍ ነገ አርብ የካቲት 29 2016 ዓ.ም ከ10:30 ጀምሮ በዋልያ መጻሕፍት ይመረቃል። በዕለቱም አንጋፋና ወጣት የሥነጽሑፍ ባለሞያዎች ሀሳቦቻቸውን ያቀርባሉ።”ግርባብ” በይዘት ደረጃ የሀሳብ መፅሐፍ እንደሆነ ተነግሯል።በ248 ገፆች ተቀንብቦ ለአንባቢያን ይደረሳል።
☑️የደራሲ ፋሲካ ሙሉ “ያልገሩትን ፈረስ” መጽሐፍ ቅዳሜ የካቲት 30 2016 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ጀምሮ በዓለም ሲኒማ ይመረቃል። በዕለቱም አንጋፋ የሥነጽሑፍ ባለሞያዎች ሀሳቦቻቸውን በመድረኩ ያጋራሉ ተብሏል።
☑️የደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ “በዓለቱ ላይ ” የተሰኘ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለአንባቢያን ይደርሳል። ደራሲ ሊዲያ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም “የምወድህ” እና “የእግዜር ዕዳ” የተሰኙ መጻሕፍትን ለአንባቢያን አድርሳለች።
☑️”አውደ ፋጎስ” 36ኛው ዙር የሀሳብ ውይይት የፊታችን አርብ የካቲት 29 2016 ዓ.ም በወመዘክር አዳራሽ ይካሄዳል።በዚህኛው ዙር “ባህል እና የኢኮኖሚ እድገት” በሚል በደራሲ ፀጋ ስለሺ መነሻ ሀሳብ ይቀርባል።ውይይቱ ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ ይካሄዳል።
☑️ገጣሚና ደራሲ በእውቀት ስዩም “እድል ነው” የተሰኘ አዝናኛ ወጎችና የጃዝ ሙዚቃዎች የሚቀረብበት ፕርግራም የፊታችን መጋቢት 1 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ አዘጋጅቷል።የዚህ ዝግጅት መደበኛ መግቢያ 400 ሲሆን ልዩ(VIP) 600 ብር ነው። ትኬቱ በሳንቲም ፔይ ዲጂታል መገበያያ ላይ መግዛት ትችላላችሁ ተብላችኋል።
☑️የሠዓሊ አሸናፊ ወልደየስ “Voyage and migration of birds” የተሰኘ የሥነጥበብ አውደርዕይ ዛሬ የካቲት 28 2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ ለእይታ ይበቃል። ይህ የሥነጥበብ አውደርዕይ እስከ መጋቢት 29 2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል።
☑️የሠዓሊ አፈወርቅ መንገሻ እና ሠዓሊ ቢንያም መንገሻ “ትንሳኤ” የተሰኘ የሥነጥበብ አውደርዕይ ነገ አርብ የካቲት 29 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ በፈንድቃ ባህል ማዕከል ይከፈታል።
አዘጋጅ: ናቲ ማናዬ
የካቲት 28 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ