እነሆ የሳምንቱ ኪናዊ መረጃዎች ቀጥሎ ይቀርባሉ
1.”ግራ ቀኝ” አስቂኝ ድራማ በምዕራፍ ሁለት ሊመለስ ነው። አርቲስት አበበ ባልቻ ፣ አርቲስት ሚካኤል ታምሬ እና አርቲስት ግሩም ዘነበ የተጣመሩበትና ተጋባዥ ተዋናኒያን የሚሳተፉበት”ግራ ቀኝ” የተሰኘ ተከታታይ አስቂኝ ድራማ የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 27 2016 ዓ.ም በፋሲካ ዕለት በምዕራፍ ሁለት ይመለሳል። ድራማውም በኢቲቪ ዜና እና መዝናኛ ቻናል ለዕይታ ይበቃል ተብሏል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/1714587967520.jpg)
2.”የፍቅር ካቴና” የተሰኘ ተውኔት ከአስር ዓመት በኃላ በድጋሚ የፊታችን ግንቦት 2 2016 ዓ.ም በዓለም ሲኒማ ወደ መድረክ ይመለሳል።በአርቲስት ወይንሸት አበጀ ፕሮዲዩስ የተደረገው ይህ “የፍቅር ካቴና” ተውኔት ድርሰትና ዝግጅቱ የአለልኝ መኳንንት ፅጌ ነው።በተውኔቱ ድርብወርቅ ሰይፉ ፣ሚኪ ተስፋዬ ፣ ወይንሸት አበጀ ፣አሸናፊ ማህሌት በተዋናይነት ይሳተፉበታል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/IMG_20240502_080112_620-655x1024.jpg)
3.ድምጻዊ ጃኪ ጎሲ ከበርካታ ዓመታት በኃላ የሙዚቃ ስራውን ለአድማጮች ሊያደርስ ነው። ድምጻዊ ጃኪ ጎሲ “አይ እድል” በሚል ርዕሰ ያዘጋጀውን የሙዚቃ ስራ በቅርቡ ለአድማጮች የሚያደርስ ሲሆን በግጥምና ዜማ ያሲን መሐመድ ተሳትፏል። የሙዚቃ ቪዲዮውን ዳይሬክት ያደረገው አማኑኤል ገብረመድህን ሲሆን ሙዚቃ ቅንብሩን ኪዱ አድማሱ ሰርቷል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/IMG_20240502_080115_299-1024x1024.jpg)
4.ድምጻዊ ባልከው ዓለሙ እና ድምጻዊት ስንታየሁ በላይ በድጋሚ የተጣምሩበት “ይገርማል” የተሰኘ ሙዚቃ የፊታችን ሰኞ ሚያዝያ 28 2016 ዓ.ም በሙዚቃዊ ሪከርድስ ዩቲዩብ ቻናል እና በዲጂታል የሙዚቃ መተግበሪያዎች ይለቀቃል። በሙዚቃዊ ፕሮዲውስ የተደረገው “ይገርማል” የህዝብ ዜማ ሲሆን በአለማየሁ ደመቀ በድጋሚ ተደርሷል። የግጥም ስራውም የአለማየሁ ደመቀ ነው። በቅንብር ግሩም መዝሙር እና በሚክሲንግ አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ ተሳትፈዋል። በቅርቡ ሁለቱ ድምጻዊያን “ከሃሳቤ” የተሰኘ የሙዚቃ ስራ ለአድማጮች ማድረሳቸው ይታወሳል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/PhotoCollage_1714626361296-1024x1024.jpg)
5.በደራሲ መስፍን ወንደሰን የተዘጋጀው “ሸሙኔ” የተሰኘ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ በቅቷል። የመጽሐፉ ይዘት የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆን ስለመጽሐፉም ገጣሚ መዘክር ግርማ በጀርባው ገፅ”አጭር ልቦለድ የቀጭታ ንባብ ከሆነ ፣ይህ ልቦለድ የቁጭ ብድግ ንባብ ነው።በጣም ከመመሰጡ የተነሳ ወይ በጣም እንስቃለን ፣ ወይ በሀዘን ተነስተን እንቆማለን፣ ወይ እንገረማለን።” በማለት ጽፏል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/IMG_20240502_080122_420-1.jpg)
6.”ሥነ ስቅለት” የተሰኘ ልዩ ዝግጅት የፊታችን ቅዳሜ ሚያዝያ 26 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ ገርጂ በሚገኘው ዓለም ጋለሪ ውስጥ ይካሄዳል። በዕለቱም “ሥነ ስቅለት”ን የሚያወሱ የሥነጽሑፍ ፣ የሥዕልና የፊልም ስራዎች ይቀርባሉ ተብሏል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/IMG_20240502_080118_218-724x1024.jpg)
7.የ”ኤንቢሲ ታለንት ሾው” ምዕራፍ ሶስት ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 18 ድረስ በየቀኑ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል ተብሏል።የምዕራፍ ሶስት “ኤንቢሲ ታለንት ሾው” ማጣሪያውን ባለፉ ከፍተኛ ልምድ ባላቸውና ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች በተወጣጡ 21 ባለተስጥዖ ድምፃውያን መካከል የሚደረግ የሙዚቃ ውድድር ሲሆን መክፈቻው የፋሲካ ዕለት ከሰዓት በኋላ ይጀመራል፡፡
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/IMG_20240502_080124_175-803x1024.jpg)
8.በኢትዮጵያ የጠልሰም ሥዕል አሳሳል ዘርፍ ውስጥ አንጋፋ የሚባሉት ሠዓሊ ሔኖክ መልካምዘር ይሁን የሙያና የህይወት ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መርሐግብር የፊታችን ረቡዕ ሚያዝያ 30 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ( TMS) ግቢ ውስጥ ይካሄዳል።በዕለቱም ስለ ጠልሰም ጥበብ ምንነት ፍልስፍናና አሰራር ፤ እንዲሁም ስለ ትምህርት ሥርዓታችን ውይይት የሚካሄድ ሲሆን በተጨማሪም በቅርቡ በሻርጃህ አርት ፋውንዴሽንና ሙዚየም የተከፈተውና እየታየ ባለው ሥራዎቻቸው ዙሪያ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/IMG_20240502_080119_960-674x1024.jpg)
9.በአሜሪካ ኒዮርክ አስራ ሶስት ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያ የሚሳተፉበት ‘Connected Threads: Contemporary Art from the Horn of Africa and Diaspora’ የተሰኘ የሥዕል አውደርዕይ ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 23 2016 ዓ.ም ይካሄዳል። በዚህ የቡድን አውደርዕይ ዳዊት አድነው፣ አዲስኪዳን አምባዬ፣ ተስፋዬ በቀለ፣ መሪኮኮብ ብርሃኑ፣ ትዝታ ብርሃኑ፣ ኖህ በየነ፣ ሄኖክ ጌታቸው፣ እንግዳዬ ለማ፣ ታደሰ መስፍን፣ ህሊና መታፈሪያ፣ ሰሎሜ ሙለታ፣ ንሪት ታከለ እና ተስፋዬ ኡርጌሳ ይሳተፉበታል።
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/1714596965957-1024x1024.jpg)
10.”የለዛ ሽልማት” የህዝብ ድምፅ መስጫ ቀን ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 23 2016 ዓ.ም ተጠናቋል።13ኛው “ለዛ ሽልማት” የፊታችን ግንቦት 16 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል (ቦልሩም) ውስጥ በደመቀ ሥነሥርዓት ይካሄደል ተብሏል::
![](https://eventaddis.com/storage/2024/05/1714597466601-1024x959.jpg)
🔴ማሳሰቢያ: በእርሶዎ ሚዲያ የኤቨንት አዲስ መረጃዎችን ሲጠቀሙ በተገቢው መንገድ ምንጭ ይጠቀሱ።
አዘጋጅ: ናቲ ማናዬ
(ሚያዝያ 24 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ )