የድምጻዊ ደሳለኝ መርሻ”ኑድኒያ” የጉራጊኛ አልበም በሚቀጥለው ሳምንት ይለቀቃል
የድምጻዊ ደሳለኝ መርሻ “ኑድኒያ “የተሰኘ 7ኛ የጉራጊኛ የሙዚቃ አልበም በሚቀጥለው ሳምንት ለአድማጮች ይደርሳል።
ይህ የጉራጊኛ አልበም 13 ትራኮችን የያዘ ሲሆን ስለፍቅር፣ ስለሃገር፣ ስለማህበራዊ ህይወት የሚዳስስ ሁለገብ አልበም ነው ተብሏል።
አልበሙ ላይ በርካታ ወጣት እና አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በግጥም እና ዜማ ራሱ ደሳለኝ መርሻ፣ ፈለቀ ማሩ፣ ናቲ ኃይሌ፣ ዘነበ መርሃባ፣ ሀብታሙ አብርሃም፣ አለማየሁ ወልዴ የተሳተፉ ሲሆን በቅንብር አሌክስ ይለፍ፣ መሀመድ ኑርሁሴን፣ ሰማገኘው ሳሙኤል፣ ፋኑ ጊዳቦ፣ ቢኒአነዴ ርሆቦት (ሮባ) የተሳተፉ ሲሆን በሚክሲንግ ሰለሞን ሃ/ማርያም፣ ፍሬዘር ታዬ፣ መሀመድ ኑርሁሴን፣ ቢኒአንዴ ተሳትፈዋል፡፡ በማስተሪንግ ሰለሞን ሃ/ማርያም በአልበሙ ተሳትፏል።
“ኑድኒያ” አልበም ግንቦት 16 2016 ዓ.ም በአርቲስቱ ዩቲዩብ ቻናልና በሁሉም ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያ የሚገኝ ሲሆን ሲዲውን ኪነት ኢንተርቴይመንት አሳትሞ ያከፋፍለዋል፡፡
አርቲስት ደሳለኝ መርሻ አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በትክክል የተመዘገበ 3.8 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ዛሬ በማርዮት ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል።
አርቲስት ደሳለኝ መርሻ በሙዚቃዎቹ የጉራጌ እሴቶችን፤ ታሪክ፤ ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚና ማሕበራዊ ሕይወትን በተባ ኪናዊ ለዛ በመሰነድ እና በማስተዋወቅ የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡
ባለፉት 20 አመታት ሙዚቃን ሕይወቱ በማድረግ ለበርካታ ድምፃውያንም ግጥም እና ዜማዎችን የሰጠው ደሳለኝ መርሻ የመጀመርያ አልበሙ ያሳተመው አዲስ አበባ ውስጥ የታክሲ ሹፌር እየሰራ ባለበት ወቅት ነበር።