የሙዚቀኛ ዕብነ ሐኪም “ብራና” ገሚስ አልበም ተመረቀ
ከዓለም አቀፉ ሶኒ ኢንተርቴይመንት አፍሪካ ጋር አብሮ በመስራት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሆነው ወጣቱ ሙዚቀኛ ዕብነ ሐኪም “ብራና” የተሰኘ ገሚስ የሙዚቃ አልበሙ በይፋ ተመርቋል።
አልበሙ በባና ሪከርድስ የቀረበ ሲሆን አቀናባሪ ኑሂ በአቀናባሪነት ፤ ሙዚቀኛ ዕብነ ሐኪም በሙዚቃ ዜማ እና ግጥም ጻሀፊነት እንዲሁም ሌሎች ወጣት እና አንጋፋ የሙዚቃ ባለሞያዎች እንደተሳተፉበት ተገልጿል።
ገሚስ አልበሙ ብራና ፣ የኔታ ፣ቃል ብቻ፣ ገላ ፣ይሁን ፣ ጉድ ነው የተሰኙ አንዱ ከአንዱ ጋር በሀሳብ የሚተሳሰሩ ስድስት የሙዚቃ ስብስቦችን ይዟል።
አልበሙ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልትን ከዘመናዊ ስልቶች ጋር በማጣመር የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮ-ፊዩዥን የሙዚቃ ስልትን የያዘ እንደሆነ ተገልጿል።
ለሁሉም ሙዚቃዎች ስድስት የሙዚቃ ቪዲዮዎች የተሰራላቸው ሲሆን አልበሙን ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ አራት ዓመት ገደማ እንደፈጀም ተገልጿል።
ገሚስ አልበሙ በ”EBNE HAKIM” በተሰኘው የሙዚቀኛው የዩቲዩብ ቻናል እና በዓለምአቀፍ የሙዚቃ ማሰራጫ መተግበሪያዎች በኩል ተለቋል።
ከተመሰረተ ሶስት ዓመታት ያስቆጠረው “ባና ሪከርድስ” አዳዲስ ባለተሰጥኦ ሙዚቀኞችን እየመረጠ የማርኬቲንግ ፣ ስርጭት እና ፕሮዳክሽን ስራዎችን የሚሰራ ሲሆን ይህም “የብራና” አልበም የመጀመሪያ ፕሮጄክታቸው እንደሆነ የባና ሪከርድስ መስራችና ስራ አስኪያጅ ብሌን መኮንን ገልጻለች።
በተጨማሪም”ባና ሪከርድስ የተመሰረተው የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ነው። በዚህም ታላቅ ኅላፊነት እንዲሁም ኩራት ይሰማናል” በማለት ተናግራለች።