አርቲስት ትዕግሥት ግርማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማህበር የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሆና ተሾመች
አለምአቀፋዊ ማህበር የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማህበር አርቲስት ትዕግሥት ግርማን የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርጎ እንደሾመ ዛሬ ሰኔ 20 2016 ዓ.ም በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ሥነሥርዓት ወቅት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሕክምና ማህበር ምስረታውን ካደረገበት ጊዜ እንስቶ ዘር፣ ቀለም ሀይማኖትም ሆነ ማንነት ያልገደበው ሰብዓዊ ድጋፍ እና አገልግሎትን በኢትዮጵያ የተለያዩ አከባቢዎች እየተዘዋወር በመስጠት ላይ የሚገኝ ማህበር ነው ተብሏል።
ማህበሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች 35 የሚሆኑ የህክምና ጉዞዎችን በማድረግ ሰብዓዊነትን ባስቀደመ ተግባሩ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰብዓዊ ግልጋሎት ሰጥቷል።
በቀጣይም ማህበሩ አቅም ለሌላቸው ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ እና የሕክምና አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሙያዊ ፍቅር እና አክብሮት የታነጸ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት፤ የህክምና አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የድጋፍ ስራዎችን በአቅም ግንባታ እና በግብዓት ማሟላት ያተኮረ ስራን ለመስራት አቅዷል፡፡
በእዚህ መነሻነትም ማህበሩ ከእዚህ ቀደም ከሰራቸው የሰብዓዊነት ስራዎች በተጨማሪ በእዚህ ወቅት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን እና ወደፊት ሊከውን ያቀዳቸውን ውጥኖቹን መነሻ በማድረግ ተወዳጇን ተዋናይት እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ አርቲስት ትዕግስት ግርማን የበጎ አድራጎት አምባሳደር አድርጎ ሾሟል።